የገዳሟ አመሠራረት

ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በአጸደ ሥጋ ባረፉ ጊዜ አጽማቸው የጸሎት ቤታቸው በነበረችው በሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ፤ ለመልካም ስራቸው መዘከርያ የሚሆን ከፍ ያለ መታሰቢያ እንዲቆምላቸው በልጃቸው በግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ሀሳብ ቀረበ፡፡ በዚህም ጉዳይ ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ያን ጊዜ አልጋ ወራሽ) ከልዑላኑ፣ ከመሣፍንቱ፣ ከታላላቆቹ መኳንንትና ባለሥልጣኖች ጋር በመካከከርና በመተባበር በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ወጪ እንዲሆን ተፈቅዶ፤ የንጉሡ የአትክልት ስፍራና መናፈሻቸው በነበረው እና በቤት መንግሥታቸው ቅጽር ውስጥ ከሚገኘው መሬት አንድ ጋሻ (400,000 ስኩዌር ሜትር) ላይ መታሰቢያቸው እንዲቆም ተወሰነ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ ሥራም በ1909 ዓ.ም. የግንባታ ቦታ ጠረጋ፣ አለቶችን በድማሚት የማፈራረሱ፣ የአፈር ቊፋሮውና መሬቱን የመደልደል ሥራ በማከናወን ተጀመረ፡፡ ብርቱ ጥንቃቄ የሚሻው መሠረቱን የማደላደሉ ሥራ ወራትን ወስዶ 1910 ዓ.ም በሊቀ ጳጳሱ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ መሪነት ምስባክ ተሰብኮ፣ ወንጌል ተነቦ ምሕላ ተደርጎ፣ ሥርዓተ ቡራኬው ከተጠናቀቀ በኋላ መሠረቱ ተጣለ፡፡

በዚህ ሁኔታ መሠረቱ የተቀመጠለት የዚህ ሕንጻ ሥራም አሥር ዓመታትን አስቆጥሮ ታኀሣሥ 3 ቀን 192ዐ ዓ.ም በዘመነ ዮሐንስ በእጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (በኋላ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ) ቡራኬ ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያኑ ተከናውኖ ከጎንደር የመጣችው ታቦተ በአታ ለማርያም ወደታነጸው ቤተክርስቲያን በክብር ገባች፡፡ በዚያው ዕለት የዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ አጽም አርፎበት ከቆየው ከሥዕል ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ወጥቶ በምድር ቤቱ በተዘጋጀላቸው ማረፊያ በክብር ገብቶ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ ታኅሣሥ 3/1906 ዓ.ም ዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ ከዚህች ዓለም በሞት የተለዩበት ዕለት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የዚህ ገዳም ስያሜውም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ፡፡

የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ሕንጻ ቤተ ክርስትያን ከመሠረት እስከ ጣራ ድምድማት በድንጋይ ብቻ የተሠራ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት እና ማንሻ ፑሊዎች/ፎርክሊፍቶች ባልነበሩበት በዚያ ጊዜ እስከ አንድ ሜትር በኀምሳ ስፋት ያላቸውን ድንጋዮች ወደ ላይ ያን ያህል ከፍታ በማንሳት ይህንን መሳይ ሕንጻ መስራት ምን ያህል ፈታኝ ሥራ ሊኾን እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይኾንም፡፡ ድንጋዮቹ ልዩ በሆነ ማጣበቂያ እየተያያዙ ስለተሰሩም በዓይን ሲሚንቶ ወይም መሰል ድንጋዮችን ለማያያዝ የተለመዱ ነገሮች የማይታዩበት ስለሆነ፤ ካለምንም ማያያዣ የተነባበሩ መስለው ለሚመለከታቸው ዕፁብ ድንቅ የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በሕንጻው ልዩ ልዩ ክፍሎች ላይ የሚታዩት በድንጋዩ ላይ የተሰሩት ቅርጻ ቅርጾችም እጅግ ጥልቅ ጥበብ የሚታይባቸው፤ በዘመን ብዛት ውበታቸው ያልደበዘዘ፤ ከመቶ ዓመታት በኋላም በአድናቆት የምንመለከታቸው እንዲሆኑ አድርጓቸ

አባቶች እንደሚናገሩት የበአታ ቤተ ክርስቲያን የተሠራበት እጅግ ጠንካራና ውብ ድንጋዮች ከቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ምሥራቃዊ ክፍል እና ኮተቤ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የሚመጡ ነበሩ፡፡ ወደግንባታው ስፍራም በጋሪ ተጭኖ በቀንድ ከብቶች ትከሻ እየተጐተተ ይመጣ እንደ ነበር እና ጋሪዎቹን ይስቡ የነበሩ ድልብ ሰንጋዎች ከዑራኤልም ይኹን ከኮተቤ ድንጋዮቹን ጐትተው ማምጣት ይችሉ የነበረው ለአንድ ጊዜ ብቻ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ከዚኽ በኋላ በድካም ብዛት ለሌላ ሥራ ያገለግላሉ ተብሎ ስለማይታሰብ እየታረዱ በግንባታው ሥራ ለተሰማሩት ሠራተኞችና ድኾች ታርደው በምግብነት ይቀርቡ እንደነበር ነው የሚነገረው፡፡ ምን ያህል ከብቶች በቤተ ክርስቲያኑ ሕንጻ ግንባታ ወቅት ታርደው እንደነበር ለመገመት በእንጦጦ ማርያም ሕንጻ ግንባታ ወቅት ለዕርድ የዋሉትን የቀንድ ከብቶች ብዛት በንጽጽር መመልከቱ ምናልባት ለግንዛቤ ይረዳን ይሆናል፡፡

ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ በሕይወት ዘመናቸው ከአሠሯቸው ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት አንዷና የመዠመሪያ የሆነችውን የእንጦጦ መንበረ ፀሓይ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግንባታዋ ሦስት ዓመታትን የወሰደ ሲኾን ሥራው ተጠናቅቆ ከአለቀና ቅዳሴ ቤቷ ከተከበረበት ዕለት ዠምሮ ለስምንት ቀን ደስታቸውን ለመግለጽ ግብዣ ሲያደርጉ የበጎችና የፍየሎች ቊጥርን ሳይጨምር 5395 በላይ ድልብ ሰንጋዎች እንደታረዱ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ‹ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ› በተሰኘው መጽሐፋቸው አስፈረውታል፡፡ ለስምንት ቀን ግብር ከ5 ሺህ በላይ ሰንጋዎች ለዕርድ ከቀረቡ ዐሥር የግንባታ ዓመታትን ለአስቈጠረው የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ሕንጻ ግንባታ ለአንድ ዙር የግንባታ ድንጋይ ከአጓጓዙ በኋላ የታረዱትን ሰንጋዎች ብዛት በመገመት፤ ለመቁጠር የሚያስቸግር ብሎ ማለፍ ይሻላል፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ግን የታዕካ ነገሥት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የላመ የጣመ ሳይቀምሱ በጾምና በጸሎት እየተጉ በዙሪያቸው ከነበሩት ካህናትና አማካሪዎቻቸው እንዲሁም ባለሟሎቻቸውና ተከታዮቻቸው ጋር በመሆን ሥራውን በቅርበት ይከታተሉ ነበር፡፡

ከድንጋዮቹ ስፋት እና ርዝመት የተነሳ ወደ ከፍታው ስፍራ ለማውጣት ከነበረው ፈታኝ ሥራ ባሻገርም የቤተክርስቲያኑ የመኻከለኛው ትልቁ ጉልላትና አራት ዶሞች ቅርጽ ማውጣት በጣም ከባድ ሥራ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይ የመኻከለኛው እንደጣራ የሚሆነው ጕልላት አኹን የሚታየውን ቅርጽ ይዞ እንዲቀር በድጋፍነት የተጠቀሙበትን የአጣናና የጣውላ መቀሰቻ ርብራብ ከሥራው ፍጻሜ በኋላ ለማፍረስ ሲታሰብ ድንጋዩ አኹን እንደሚታየው በአየር ላይ ጸንቶ ላይቀር ይችላል፤ ድጋፎቹ ከሥሩ ሲፈርሱ ይናድ ይሆናል የሚል ስጋት በሰፊው ሰፍኖ ነበር፡፡ ንግሥቲቱም ይኽ ስጋት ከገባቸው ሰዎች መኻከል አንዷ ስለነበሩ፤ የድጋፍ ቀስቶቹ ከመፍረሳቸው አስቀድሞ በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ አንድ ሱባዔ ምሕላ እንዲያዝና ጸሎት እንዲደረግ ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር ይባላል፡፡

ሕንጻው እንደፈሩት ሳይሆን፤ እጅግ ባማረ ሁኔታ መጠናቀቁን ባዩ ጊዜ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ያለምንም ፍርሀት ወደ ጕልላቱ አናት ላይ ወጥተው በ4ቱም ማዕዘን ተዟዙረው ሰግደውና ጸልየው ሦስት ጊዜ እልል ብለው እንደወረዱ ይነገራል፡፡ የሕንጻው ግንባታ ተጠናቅቆ ቅዳሴ ቤቱ ከከበረ በኋላ ቀጣዩ ክረምት ከመድረሱ አስቀድሞ አምስቱም ዶሞች በርሳስ ሊድ እንዲሸፈኑ እና ብርማ ቀለም እንዲቀቡ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት በዐምስትና ስድስት ወራት ውስጥ በሊድ ተሸፍነው እና ብርማ ቀለም ተቀብተው ተጠናቀቁ፡፡ አራቱ ትንንሽ ውብ ዶሞች ከመኻከለኛው ትልቁ ዶም ላይ ካለው የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘውድ ቅርጽ ካለው ወርቅ ቅብ ጉልላት ጋር በአንድ ላይ ሲታዩ ውበታቸው ፍጹም ሐሴትን የሚያጎናጽፍ ሆነ፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ በአራቱ አቅጣጫ የምናገኛቸው የሰሎሞናውያን ንግሥናን የሚያመለክቱ ስምንት የአንበሳ ቅርጽ ያላቸው የነሐስ ምስሎችም ተጨማሪ የሕንጻው ሞገስና የምድረ ግቢው ውበቶች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጡም እንዲሁ ለመሬቱ ከተነጠፈው የሸክላ ወለል ጀምሮ፣ እስከ መብራትና መጋረጃ ድረስ ያሉት ነገሮች ፍጹም በሆነ ጥንቃቄ ተመርጠው የተሰሩ መሆናቸውን ማንም አይቶ ሊመሰክረው የሚችል ነው፡፡ ተፈጥሮዊ ብርሃንና አየር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በተለይም ወደምድር ቤቱ እንዲገባ የተደረገበት መንገድ አስገራሚ ነው፡፡

በቅድስቱ ውስጥ ወደላይ ስናንጋጥጥ የምንመለከተው ደግሞ እንደጣራ የሆነው የዶሙ የውስጠኛ ክፍልም የቤተክርስቲያንን ሰማያዊነትና እግዚአብሔር በመንበረ መንግሥቱ መኖሩን ለማመስጠር እውነተኛውን ሰማይ መስሎ ቀብቶ፤ ከዋክብቱ በላዩ ላይ ተሥለው ሲታይ ጣራው ቀርቶ ቀጥታ ሰማይ እያየን እንዲመስለን የሚያደርግ ጥበብ የሚታይበት ነው፡፡ ከዚህም ስር ባሉ አራቱ ማዕዘናት በልዩ ጥበብ፤ በዘመኑ ዕውቅ ሠዐሊያን የተሰሩ ሥዕላትን እናገኛለን፡፡

በምዕራብ በኩል ዳግማዊ ዐፄ ሚኒልክ ከአቡነ ማቲዎስ እጅ ቅብዐተ መንግሥት ተቀብለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሆኑበት ንግሥና ሥርዐት የሚያሳይ ስዕል፤ በስተምስራቅ በኩል ንግሥት አዜብ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የሰሎሞንን ዜና ጥበቡን ሰምታ እጅ መንሻ ይዛ ብዙ ሕዝብ አስከትላ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድዋን የሚገልጽ ሥዕል፤ በስተሰሜን በኩል በ1888 ዓ.ም. በታላቁ የአድዋ ጦርነት ጊዜ የኢትዮጵያ ጀግኖች ከሰማዕቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነት በፋሽስት ጣሊያን ጦር ላይ ያገኙትን ድል፤ የጦር መሪው ልዑል ራስ መኮንን ለአፄ ምኒልክ ሲያስረዱ የሚያሳይ ሥዕል ሲኖር፤ በስተደቡብ ደግሞ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጽያ የሐረርጌን ክፍለ ሀገር ለልዑል ራስ መኮንን ፈቅደው የአስተዳዳሪነቱን ሥልጣን በክብር ሲሰጧቸው የሚያሳዩ ሥዕሎች ናቸው፡፡

የቤተክርስቲያኑ ስራ ከተጠናቀቀ በኋላም ከንግሥቲቱ በተጨማሪ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ቤት ለሆነው ለዚህ ገዳም መቋቋሚያ የሚሆን ብዙ ርስት ጉልትና ሰፊ የከተማ ቦታዎችን ሰጥተዋል፡፡ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ስምም ብዙ መጻሕፍትን አጽፈውም በስጦታ አበርክተዋል፡፡ መታሰቢያቸው በመቆሙ ደስ ከተሰኙና በርካታ ስጦታዎችን ካበረከቱ መኳንንቶቻቸው መካከል ፊታውራሪ ሀብተ ጊዩርጊስ ዲነግዴ /አባ መላ/፣ አሳላፊ ኃይለ ኢየሱስ፣ ንቡረ ዕድ አድማሱ፣ ሐኪም ታችበሌ፣ ቀኝ አዝማች ወልደ ሚካኤል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ክብረ በዓል የነበረዉን የደስታ ድባብ ሳይደበዝዝ፤ በተለይም ከየጠቅላይ ግዛቱ በንግሥቲቱ አፈላላጊነት በበአታ በተሰባሰቡ ሊቃውንት ይደርስ የነበረውን ስብሐተ እግዚአብሔር፤ ይፈስ የነበረዉን የቅኔ ማዕበል አይተው ዘለቄታዊነት እንዲኖረው ያሳሰባቸው አባ ገብረ አብ መንግሥቱ የተባሉ ታላቅ የቤተ ክርስቲያኗ አባት በሌላ ሀሳብ ወደ ግርማዊት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ፊት ቀረቡ፡፡ ለንግስቲቱም እንዲህ አሏቸው ‹ግርማዊት ሆይ እግዚአብሔር በዕድሜ፣ በጤና ይጠብቅዎ ለትውልድ የሚተርፍ መልካም ሥራ ሠርተዋል፡፡ ዋጋዎ በሰማይ እንጂ ከዚኽ ከኃላፊው ዓለም እንዳልኾነ ተገንዝበው ይኽን የመሰለ ቤተ እግዚአብሔር ሠርተው ሲያበቁ ያለ አገልጋይ የተዉት እንደኾነ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ማስወቀሡ አይቀርም፡፡ ዛሬ በዙሪያዎ በአሰባሰቧቸው ሊቃውንት ይኽ ቤተ ክርስቲያን ያለ አንዳች ችግር ሊገለገል ይችላል፡፡ ነገር ግን በጤና፣ በኑሮና በዕድሜ ጕዳይ የሊቃውንቱ ቊጥር እየቀነሰ ሊኼድ እንደሚችል ዐስበው፤ ይህ እንዳይከሠት መፍትሔ ሊያበጁለት ይገባል ብለው በማሳሳባቸው ምክንያት፡፡› አስተዋይቱ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱም አባ ገብረ አብ መፍትሔ ብለው ያቀረቡትን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት (አብነት ት/ቤት) የማቋቋም ሐሳብ ተቀብለው፤ ለብዙ ሊቃውንት መፍለቂያ የሆነውን የመጀመሪያውን የዓመት ልብስ፤ የዕለት ጉርስና ማደሪያ ለተማሪዎች እየሰጠ የሚያሰለጥነውን ‹የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት› ለመስራት ወሰኑ፡፡

 ይህችን ድንቅ ቤተ ክርስቲያን ያሳነጹት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ (ወስመ ጥምቀታ አስካለ ማርያም) በአገራችን ታሪክ የመጨረሻዋ ንግሥተ ነገሥታት የሚል ማዕረግ የተሰጣቸው ሰው ናቸው፡፡ ከ1909 – 1922 ዓ.ም. ለዐሥራ ሦስት ዓመታት ያኽል ዘውድ ደፍተው በመንበረ ንግሥናው ላይ ተቀምጠው በርካታ ተግባራትን ያከናውኑ ቢኾንም ብዙ ያልተነገረላቸውና ያልተዘመረላቸው እንስት መሪ ናቸው፡፡ ከሀገር መሪነትና የፖለቲካ ተሳትፎ ባሻገር በተለይ በእስራኤል ሀገር በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርዶቶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳምንና አገልጋይ መነኮሳቱን በገንዘብ ከመደገፍና በኀሳብ በማበረታት፤ በሀገር ውስጥ በዐዲስ አበባና በመላው ሀገሪቱ ያረጁ አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ በማነጽ፤ ዐዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትንም በብዛት በመገንባት ያገለግሉ የነበሩ ንግሥት መሆናቸውን ታሪክ ሲያስታውስ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ስማቸውን በጸሎት እስከ ዓለም ፍጻሜ ሲጠራ ይኖራል፡፡