የገዳሟ ቤተ-መዘክርና ሌሎች የጉብኝት መስህቦች

የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያምና የደብረ መንክራት ሥዕል ቤት ኪዳነምሕረት ገዳም በዐዲስ አበባ መስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ዕውቅና ከተሰጣቸው ጥቂት የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ይህ ገዳም በመኸል ዐዲስ አበባ አራት ኪሎ፤ ከቤተ መንግስት፣ ከግቢ ቅ/ገብርኤል ቤተክርስቲያን እና ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አጥር ተጋርቶ በመካከል ላይ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡ ገዳሙን የቱሪስት መዳረሻ፣ ሊጎብኝ የሚገባው ስፍራ ነው ተብሎ ዕውቅና እንዲያገኝ ያደረጉት በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊ፣ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ እንዲሁም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ይዟል፡፡ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

1. የዳግማዊ አጤ ምኒልክ የጸሎት ቤት (ደብረ መንክራት ሥዕል ቤት ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን)

ሥዕል ቤት ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን በገዳሙ ከሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች አንዷ ናት፡፡ በ1879 ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት ይህች ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የምንሰጣቸው የዳግማዊ አጤ ምኒልክ የጸሎት ቤት የነበረች ነች፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን በእቴጌ ጣይቱ ከቤተመንግስቱ ጋር አብራ የተሰራችና፣ ቀደም ባለው ዘመን የቤተመንግስቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ የነበረች ታሪካዊ ቦታ ነች፡፡ መጀመሪያ ለጸሎት ቤትነት የተሰራች ብትሆንም በኋላ ታቦት ኪዳነምህረትን ዳግማዊ አጤ ምኒልክ እንድትገባ በማድረግ ቤተክርስቲያን እንድትሆን አደረጉ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም እስካዛሬ በርካታ ገባሬ ተአምራት ሲታይባት የኖረች ቦታ ሆናለች፡፡

ይህች ቅልብጭ ያለች መሶበወርቅ መሳይ፣ ለዓይን ማራኪ ቤተ መቅደስ፤ ከ130 ዓመታት በላይ እድሜ ያላት ከመሆኗም ባሻገር የታላቁ ንጉስ የዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ የንግሥት ጣይቱ፣ የመኳንንቱና መሳፍንቱ የዘወትር ጸሎት ማድረሻ ስፍራ የነበረች ታሪካዊ ቦታ ነች፡፡

የሥዕል ቤት ኪዳነምሕረት እና በአታ ለማርያም ህንጻ ቤተክርስቲያናት የታነጹበት አጸድ ራሱም ታሪካዊ ነው፡፡ ንግሥተ ነገሥታ ዘውዲቱ ለአጤ ምኒልክ ለመልካም ሥራቸው መታሰቢያ እንዲሆን የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲያሰሩ ለአባታቸው ሁነኛ መዘከሪያ ይሆን ዘንድ ይህንን የአባታቸውን የአትክልት ቦታ የነበረውን አጸድ መርጠዋል፡፡ ስለሆነም የገዳሙን ቅጽረ ግቢ ንጉሱ የአትክልት ስፍራ የነበረ ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

2. የዳግማዊ አጤ ምኒልክ እና የሌሎች ነገሥታት መካነ መቃብር

ሌላው ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የገዘፈ ታሪካዊ ስፍራ የሚያደርገው የነገሥታቱ ዐጽም በክብር ያረፈበት ስፍራ መሆኑ ነው፡፡ የኢትየጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነው የአድዋ ድል መሪ፣ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት የዳግማዊ አጤ ምኒልክ መካነ መቃብር መገኛው የታዕካ ነገሥት ቤተ ክርስቲያን ምድር ቤት ነው፡፡ የዳግማዊ አጤ ምኒልክ ባለቤት፣ የአድዋ ድል ቁልፍ ሰው የእቴጌ ጣይቱ አጽምም ከባለቤታቸው ጎን በዚሁ ስፍራ በክብር አርፎ ይገኛል፡፡ የመጨረሻዋ የኢትዮጵያ ንግሥት፤ ንግሥተ ነገሥታ ዘውዲቱ ምኒልክ መቃብርም በዚያ ነው፡፡ የግብጻዊው ጳጳስ የአቡነ ማቲዎስ እና የንጉሥ ቀዳማዊ ኀይለስላሴ ልጅ የልዕልት ፀሐይ መካነ መቃብሮች መገኛ ታሪካዊ ስፍራም ይህ ገዳም ነው፡፡ የእነዚህ የሀገር አውራዎች መካነ መቃብሮች ባማረ እምነ በረድ ተሠርተው ሲታዮ፤ ከታሪክ ባሻገር ለጎብኚዎች የዘመኑን የእምነበረድ ላይ ጥበብ የት ድርሶ እንደነበር የሚያሳዩ ቋሚ ምስክሮች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

3. የመጀመሪያው የመታሰቢያ ተቋም (foundation) እና የአረጋውያን መርጃና የእጓለማውታን ማሳደጊያ ድርጅት

የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የተመሠረተው የእምዬ ምኒልክን በጎ ስራ የሚዘክር ቋሚ ምስክር እንዲሆን ነው፡፡ ይህ በዘመናችን foundation ብለን የምጠራው አይነት ድርጅት ሲሆን፤ አሁን አሁን በበርካታ ታዋቂና መልካም ሰዎች ስም የሚመሰረት ቢሆንም ከዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ድርጅት የቀደመ ስለመኖሩ ማስረጃ የለምና፤ ምናልባትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መታሰቢያ ድርጅት (foundation) ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል፡፡ ይህም ሌላዊ የታሪካዊነቱ መገለጫ ነው፡፡ ይህ መታሰቢያ ድርጅትም ከቤተ ክርስቲያኑ በተጨማሪ የመጀመሪያውን ዘመናዊ አደረጃጀት ያለው የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ት/ቤት የያዘ ነው፡፡
ከ1922 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው በኢትዮጵያ ቀዳሚ እንደሆነ የሚታመነው የአረጋውያን መርጃና የእጓለማውታን ማሳደጊያ ድርጅትም ለዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያነት የተቋቋመው የዚህ ገዳም አንድ ክፍል ነው፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በበጀት እጥረት ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል አገልግሎት እየሰጠ ባይሆንም፤ ይህ ተቋም ከ1922 ዓ፣ም. ጀምሮ በርካታ አረጋውያን ተጡረውበታል፣ በርካታ አሳዳጊ ያልነበራቸው ልጆች አድገውበት ለወግ ለማዕረግ በቅተውበታል፣ በዘመኑም ትልቅ የማህበራዊ ክፍትትን ሞልቶ ዛሬ ላይ ለምናገኛቸው መሰል ድርጅቶች ምሳሌ በመሆን አገልግሏል፡፡

4. ታሪካዊ ንዋያተ ቅድሳትና የነገሥታቱ የወግ ዕቃዎች

በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ለጎብኚዎች መስህብ ከሆኑ ቅርሶች መካከል እንደሙዚየም በሚያገለግለው ምድር ቤት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ንዋያተ ቅድሳት፣ የብራና መጻሕፍት እና የነገሥታቱ የወግ ዕቃዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በብዙ ቦታዎች እምብዛም የማይገኙ እንደጊዮርጊስ ወልደሐሚድ፤ መጽሐፈ ሄኖክ፣ መጽሐፈ ብርሃን፣ መጽሐፈ ጥበብን የመሰሉ በርካታ የብራና መጻህፍት በገዳሙ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በስጦታ ለነገሥታቱ የተበረከቱ በ15ተኛው ክ/ዘ የኖረው የእውቁ ጣልያናዊ ሰዐሊ ሚካኤል አንጀሎ ስራ የሆነው የእመቤታችን ምስል (ምስለ ፍቁር ወልዳ)፣ በ1924 ዓ.ም. ከግሪክ መንግሥት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በስጦታ የተበረከተ የኢየሱስ ክርቶስ ሥነ-ግንዘቱን የሚሣይ ልዩ ምስል፣ ከሩስያው ጳጳስ ለዳግማዊ አጼ ምኒልክ በስጦታ የተበረከተ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምስል፣ ከታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የመጡ ከሶስት መቶ አመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ የሸራ ላይ መንፈሳዊ ስዕሎች እና ሌሎች የቅዱሳን ምስሎች ተጠቃሽ የቤተክርስቲያን እና የሀገር ቅርሶች ናቸው፡፡
በከበሩ ማዕድናት የተሰሩ ጽንሐዎች፣ መስቀሎች፣ ጽዋዎች፣ ጸናጽል፣ መቋሚያና ከበሮ፣ የተጌጡ መጎናጸፊዎች፣ ድባበቦች በገዳሙ ከሚገኙ የከበሩ ንዋየ ቅድሳት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
የታላላቅ ታሪክ መዘክሮች ከሆኑ የነገሥታቱ ዕቃዎች መካከልም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አድዋ ሲዘምቱ ይዘዋት የሄዱት “ድል አድራጊ” የምትሰኘው ወንበር፣ የአድዋ ዘመቻ ክተት የተጠራበት ነጋሪት/ከበሮ፣ ድባብ፣ ንጉሱ ይጸልዩበት የነበረ የብራና ዳዊት፣ የብር ዘውዶች፣ ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ በስጦታ የተሰጡ የዙፋን ወንበሮች የጎብኚዎችን ቀልብ ከሚይዙ ቅርሶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቤተክርስቲያኒቱን ካሣነጹት ከንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የወግ ዕቃዎች መካከልም የክብር ካባቸው፣ ይጸልዩበት የነበረ የብራና ዳዊት፣ ከብር የተሰራ ጠበል መጠጫቸው፣ ውዳሴ ማርያም ሲደግሙ የሚቀመጡበት ወንበር ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

5. ልዩ የኪነ ህንጻ ጥበብ

ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳምን እንደአንድ የቱሪስት መዳረሻ እንዲጠቀስ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የቤተክርስቲያኒቱ ሕንጻ ልዩ የአሰራር ጥበብ ተጠቃሽ ነው፡፡ እጅግ ውብ የሆነው ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያውያንን ሕንጻ አሠራር ዘይቤንና የዐጤ ምኒልክን የቤተ መንግሥት ፈለግ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ በአራቱ አቅጣጫ የሰለሞናውያን ንግሥናን የሚያመለክቱ ስምንት የአንበሳ ቅርጽ ያላቸው የንሐስ ምስሎች ለሕንጻው ሞገስ ሆነው ይታያሉ፡፡
የቤተክርስቲያኑ ሕንጻ ጣራውን (ዶሙን) ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በልዩ ጥበብ በተጠረቡ በአማካይ አንድ ሜትር የሚረዝሙ ግዙፍ ድንጋዮች የታነጸ መሆኑን ስንመለከትም፤ ከመቶ አመት በፊት ይህን መሳይ ጥበብ መኖሩን እንድናደንቅ የሚያደርግ ነው፡፡ ለግንባታ የዋሉት ድንጋዮች በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተመረጡ፣ ልዩ በሆነ ማጣበቂያ እየተያያዙ በግንባታ ላይ የዋሉ መሆናቸውን በማየት ብዙዎች ካለስሚንቶ እንዴት ሊሆን ቻለ ብለው እንዲደነቁ፣ አንዳንዶች ደግሞ በሰጎን ዕንቁላል በስንዴ ዱቄት ተጣብቆ የተሰራ ነው ብለው እንዲተርኩ አድርጓቸዋል፡፡ በሕንጻው ልዩ ልዩ ክፍሎች ላይ የሚታዩት የድንጋይ ላይ ቅርጻ ቅርጾች ደግሞ በእንዲህ አይነት ጠንካራ ድንጋይ ላይ በዘመናዊ ማሽኖች እንኳን ለመስራት ያለውን አስቸጋሪነት ለሚያውቁ የዘመናችን የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎችን ጭምር የሚያስደንቁ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
በውስጠኛው የቤተክርስቲያኑ ክፍል በአራቱም ማዕዘን የሚገኙት ታሪካዊ ስዕሎች፣ ባለረቂቅ ጥበብ የመስኮት መስታወቶች፣ በአጠቃላይ የሕንጻው አቀማመጥና ውስጣዊና ውጫዊ አሰራር ለዘመናችን የኪነህንጻ ባለሙያዎች ማስተማሪያ፤ ለጎብኚዎች እጅግ ማራኪ ሆኖ ከመቶ አመት በላይ ዘልቋል፡፡

6. ተፈጥሮአዊ መዘክሮች

በበአታ ግቢ ውስጥ ካሉ ሀብቶች መካከል እድሜ ጠገብ ዛፎች ተጠቃሽ የተፈጥሯዊ መዘክሮች ናቸው፡፡ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት እነዚህ ሀገር በቀል ዛፎች በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተተከሉና በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተቋቁመው እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ስለሆነም ለሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ውድ ሀብቶች፤ የሚጎበኙ መዘክሮች ናቸው፡፡ ከደብረ መንክራት ኪዳነምህረት ቤተ/ክ ፊት ለፊት ላይ (በሴቶች በር በኩል) ያሉ የወይራ ዛፎች፣ በበዓታ ቤተ ክርስቲያን ቤተልሔም አከባቢና በወንዶች መግቢያ በኩል የምናገኘቸው የሾላ ዛፎች፣ እንዲሁም በተለያየ ስፍራ የምናገኛቸው የግራር፣ የሀበሻ ጽድና ሌሎችም ዛፎች የስነዕጽዋት ተመራማሪዎችና የሌሎችም ጎብኚዎችን ቀልብ ሊገዙ የሚችሉ መስህቦች ናቸው፡፡

ከታሪካዊ ቅርሶች ባሻገር የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳምን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የማይዳሰሱ ቅርሶቿ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የገዳሙ ሊቃውንት፤ በነዚህ ሊቃውንት ፊት አውራሪነት የሚከናወነው የቤተ/ክ አገልግሎት እንዲሁም በመንፈሳዊ /የአብነት/ ትምህርት ቤቱ የሚሰጠው ትምህርት በአታን በመላው ሀገሪቱ የታወቀና የተከበረ፤ የሊቃውንት ቦታ ያሰኙዋት ቅርሶቿ ናቸው፡፡
የመጀመሪያው አዳሪ የአብነት ት/ቤት፤ ስምንቱ ጉባኤያት በአንድ ቦታ ተሟልተው የሚሰጡበት፤ 28 ሊቃነ ጳጳሳትን እና በርካታ መምህራንና ቀሳውስትን ያፈራና እያፈራ ያለ ገዳም መሆኑም የሀገርና የቤተክርስቲያን ቅርስነቱን ከፍ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ይካተታሉ፡፡ ይህ የአብነት ት/ቤት በተለይ ለዘመናዊው የኢትዮጵያ ትምህርት ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ሀብቶች ያሉት ነው፡፡ ከነዚህ መካከል እያንዳንዱ ተማሪ በራሱ ፍጥነትና ችሎታ መማር እንዲችል የሚግዝ የትምህርት ስርዓት መኖሩ፣ ተማሪዎች እርስበርስ እየተማመሩ፣ የቀሰሙትን እውቀት እንዲያዳብሩ የሚደረግበት ሂደት፣ መምህራን ከስር ጀምሮ ተግባራዊ ልምምድ እያደረጉ የሚወጡበትና መሰል ሥርዓቶች ሁሉ ሊጠኑ የሚገባቸው የማይዳሰሱ የቤተክርስቲያን ቅርሶች ናቸው፡፡
እነዚህን መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮዊ ቅርሶች ከቅዳሴ ሰዓት ውጪ ባሉት ሰዓቶች፣ በማንኛውም ቀን ለጎብኚ ክፍት ናቸውና ትጎበኙ ዘንድ ገዳሙ ጥሪውን ያቀርባል፡፡