እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት መታሰቢያ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ዕለት መታሰቢያ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በአዲስ አባባ ከተማ፤ ቤተ መንግሥት አጠገብ በምትገኘው፤ ጥንታዊና ልዮ የበረከት ቦታ በሆነችው፤ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም እና ደብረ መንክራ ስዕል ቤት ኪዳነ ምህረት ገዳም ታህሣስ 3/2014 ዓ.ም. በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ፡፡ በዕለቱም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የገዳሟ ሊቃወንት፣ ታላላቅ አባቶችና እናቶች፣ እንዲሁም እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን በመገኘት በዓሉን አክብረዋል፡፡
ይህ ቀን የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ (ወስመ ጥምቀቱ ሣሕለ ማርያም) በሞተ ሥጋ ያንቀላፉበት 108ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ እንደመሆኑም፡ መካነ መቃብራቸው በሚገኝበትና ለመታሰቢያቸው በተሰራው በዚሁ ገዳም ጸሎተ ፍትሀት ተከናውኖላቸዋል፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጃቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ (ወስመ ጥምቀታ አስካለ ማርያም) የአባታቸው መልካም ስራ ይዘከርበት ዘንድ ይህን ገዳም በ1910 ዓ.ም. በጸሎትና በትጋት እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡
ዳግመኛም ይህ ቀን የእምዬ ምኒልክ የጦር አበጋዝና የቅርብ ወዳጅ የሆኑት፣ ይህ ገዳም ሲመሠረት በርካታ ንብረታቸውን ለገዳሙ ማቋቋሚያ ያበረከቱት የርዕሰ መኳንንት፣ ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (ወስመ ጥምቀቱ ኃብተ ጊዮርጊስ) ዕለተ ዕረፍት ነው፡፡
የእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ከሁላች ጋር ይሁን አሜን
ታህሣስ 3/2014 ዓ.ም.