ቴክኖሎጂ እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት

የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ተግባቦት ክፍል፣ ከመሠረተ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት እና ‘አጥቢያ ዶት ኮም’ ከተባለ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለቤተክርስቲያን ከሚያቀርብ ዓለምአቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር “ቴክኖሎጂ እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ዐውደ ጥናት ትናንት ጥር 14/2015 ዓ.ም ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ተከናወነ።

በዐውደ ጥናቱ ላይ የገዳሟ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የገዳሟ ተግባቦት ክፍል አባላት እንዲሁም የመሠረተ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት አምራርና በልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ የሚያገልግሉ አባላት ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት አመራር አባላትና ከአዲስ አበባ ሰ/ት/ቤቶች የተወከሉ አባላትም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ዘመኑ ያፈራቸውን ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን እና የመገናኛ ብዙሃንን (ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ) ሥልታዊ በሆነ መልኩ በመጠቀም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስፋፋትና በተለይም ለወጣቱ ቃለ እግዚአብሔርን ተደራሽ ለማድረግ ያለውን ጠቀሜታ፤ እንዲሁም አጠቃቀሙን ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ጋር በማይጣረስ መልኩ እንዴት ማከናወን እንደሚቻል በአይሲቲና ተግባቦት ዘርፍ የረዥም ዓመት ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ተሳታፊ በነበሩ አባቶችም መሰል ስልጠናዎች መጠናከር ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማስፋፋት ቴክኖሎጂና የሕዝብ ግንኙነት ስራን በሚገባ ለማከናወን በስፋት የሚስተዋሉ የግንዛቤና ክሒሎት ክፍተቶችን በመሰል ስልጠናዎች መሙላት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“አጥቢያ ዶት ኮም” የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማቅረብ የሚታወቅ ዓለም አቀፍ ተቋም ሲሆን፤ የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ድረ ገጽን (https://beatalemariam.org) ጨምሮ አስራ ሶስት ድረ ገጾችን ለተለያዩ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም ለሌሎች የቤተክርስቲያን አካላት የሰራ ተቋም ነው፡፡ ከቀናት በፊት ይፋ የሆነው የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ድረ ገጽ (https://eotceth.org) በዚሁ “አጥቢያ ዶት ኮም” በተባለው ተቋም የተሰራ ነው፡፡