እንኳን ኪዳነምህረት ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችኹ!

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳን የተቀበለችበት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓለ ንግሥ በገዳማችን ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም ውስጥ በምትገኘው ደብረ መንክራት ስዕል ቤት ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ዕለት የካቲት 16/2015 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል። በገዳሟ ሥርዓት መሠረት በዓቢይ ጾም ወቅት ከበሮ አይመታምና፤ ከማህሌቱ ጀምሮ እስከ አውደ ምህረቱ ያለው መዝሙር ከበሮ ሳይመታ፣ ጸናጽል ሳይንጸለጸል በመቋሚያ ብቻ በመዘመም ስብሐተ እግዚአብሔርን በማድረስ ተከብሯል።

ደብረ መንክራት ስዕል ቤት ኪዳነምህረት ቤተ ክርስቲያን የንጉሠ ነገሥቱ የአጼ ዳግማዊ ሚኒልክ ጸሎት ቤት የነበረች፤ ኋላም ታቦተ ኪዳነ ምህረትን አስገብተው የነገሥታቱና የመኳንንቱ ማስቀደሻ ሆና የኖረች ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ነች።

መዝሙራት

ኪዳንኪ ኮነ፤ ለኃጥአን ተስፋነ ኪዳንኪ ኮነ።

ትርጉም፡ እመቤታችን ሆይ ቃል ኪዳንሽ ለኛ ለኃጥአን ተስፋችን ኾነ።

ክንፈ ርግብ በብሩር ዘግቡር፣ ወገበዋቲሃኒ በሐመልማለ ወርቅ፤
አንቲ ምሥራቅ ወወልድኪ ፀሀየ ጽድቅ፣ ምሥራቅ ታዕካ ነገሥት

ትርጉም፡ ክንፎችሽ በብር ያጌጡ፣ ጎኖችሽ በወርቅ አመልማሎ የተሰሩ፤
አንቺ ምስራቅ(የጸሐይ መውጫ) ነሽ ልጅሸም እውነተኛ ፀሐይ፤ የፀሐይ መውጫ ታዕካ ነገሥት

ጼጥሮስኒ ይቤ በውስተ ውግዘት ምድር ሰናይት ኢትዮጵያ ወአኮ ከመ ምድረ ሮም፤
ምድር ሰናይት ደብረ መንክራት እንተ ዘልፈ ይሔውጻ እግዚአብሔር በማርያም ድንግል እም ዓመት እስከ ርእሰ ዐውደ ዓመት፤

ትርጉም፡ ጴጥሮስ እንዲኽ አለ ኢትዮጵያ መልካም ምድር ናት እንደሮም ምድርም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ ውብ መልካም ናት ሲል ጼጥሮስ በውግዘቱ ውስጥ እንደተናገረ፡፡
ከዓመቱ መነሻ እስከ ዓመቱ ዙሪያ ራስ (ከዓመቱ መዠመሪያ እስከ ዓመቱ ፍጻሜ) በድንግል ማርያም ረድኤት እግዚአብሔር ዘወትር የሚጎበኛት ደብረ መንክራት መልካም ናት፡፡